በዓለም አቀፍ ገበያ የወርቅ ዋጋ ማክሰኞ ዕለት (የካቲት 10፤2018 ዓ.ም.) ከ2 በመቶ በላይ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጠ። ለዚህ የዋጋ መቀነስ ዋነኛው ምክንያት የአሜሪካ ዶላር መጠናከር እና በዋና ዋና የዓለም ገበያዎች ላይ የታየው የንግድ ልውውጥ መቀዝቀዝ መሆኑ ተጠቁሟል።
የወርቅ ዋጋ በአውንስ 4,898 ዶላር አካባቢ ዝቅ ብሎ የዋለ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ሳምንት ወዲህ የታየ ዝቅተኛው ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል።
በተለይም በቻይና እና በሌሎች የእስያ ሀገራት የጨረቃ አዲስ ዓመት በዓል በመከበሩ እንዲሁም በአሜሪካ የፕሬዝዳንቶች ቀን ዝግ በመሆኑ፣ በገበያው ላይ የሚታየው የንግድ ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ለዋጋው መውረድ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚካሄደው የኒውክሌር ድርድር በጄኔቫ ዳግም መጀመሩ በጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት ምክንያት የነበረውን ስጋት በማርገቡ፣ ወርቅ እንደ አስተማማኝ መጠለያ የነበረውን ፍላጎት በትንሹ እንዲቀንስ አድርጎታል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ባለፈው ጥር ወር ያካሄደው ስብሰባ ቃለ-ጉባኤ ነገ ረቡዕ ይፋ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም ወደፊት ስለሚኖረው የወለድ መጠን አቅጣጫ ፍንጭ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የወለድ መጠን ይቀነሳል የሚለው ግምት ወደ ሰኔ ወር መገፋቱ ዶላር እንዲጠናከርና በዶላር የሚሸጡ እንደ ወርቅ ያሉ ማዕድናት ደግሞ ዋጋቸው እንዲቀንስ ማድረጉ ተመልክቷል።
ከወርቅ በተጨማሪ የብር፣ የፕላቲነም እና የፓላዲየም ዋጋም በተመሳሳይ መልኩ የቅናሽ አዝማሚያ አሳይተዋል።@SECO


