በኢቢቪ ዘጋቢ
ዳሸን ባንክና ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) በኢትዮጵያ ለሚገኙ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት የፋይናንስ አቅርቦት ለማሳደግ እና የሥራ ፈጠራን ለመደገፍ የሚያስችል አጋርነት መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።
በሁለቱ ተቋማት የአጋርነት ትብብር መሰረት አይኤፍሲ ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጎልበት የሚያስችል ትብብር የሚያደርግ ሲሆን፣ በተለይም በግብርና ንግድ ዘርፍ ውስጥ ላሉ እና በሴቶች ባለቤትነት በሚመሩ ንግዶች ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ተነግሯል፡፡
አይኤፍሲ ከዳሸን ባንክ ጋር በመጣመር ይፋ ያደረገው ትብብርም ዋነኛ ዓላማው ዳሸን ባንክ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማትን አስመልክቶ የሚተገብረውን የንግድ ሞዴል ለማጠናከር፣ የሽያጭ አቅሙን እና የገበያ ሽፋኑን ለማስፋት፣ የብድር ዋስትናውን እና የአደጋ አስተዳደር አቅሞችን በማጎልበት ዘላቂ እድገትን በማጠናከር ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡
በትብብር ስምምነቱ መሠረት፣ አይኤፍሲ(IFC) ለዳሸን ባንክ የ10 ሚሊዮን ዶላር ሪስክ የመጋራት ዋስትና (Risk Sharing Guarantee) የሰጠ ሲሆን፣ይህም ዳሸን ባንክ በሚሰጠው እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ብድር ፖርትፎሊዮ ላይ የዳሸን ባንክን እስከ 50 በመቶ የሚደርስ የብድር ስጋት የሚሸፍን ይሆናል።
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ እንደተናገሩት ወሳኝ የአደጋ መጋራት ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን እና የግብርና ተኮር ቢዝነሶችን ለመደገፍ ያለን ቁርጠኝነት ወሳኝ እርምጃን ይወክላል።

“ቁልፍ የብድር ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማጎልበት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና በመላ አገሪቱ የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ እንጥራለን ሲሉ ተናግረዋል።
ስምምነቱም የባልኩን ግልጽ የሆኑ የብቁነት መስፈርቶችን፣ ቀልጣፋ ሂደቶችን እና ትኩረት የተደረገባቸውን የፖርትፎሊዮ አስተዳደርን በመጠቀም፣ የአገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞችን የመደገፍ አቅም ከማሳደጉም በላይ አደጋን በመቀነስ ዋና ተልዕኮው ላይ እንዲያተኩር ያስችለዋል ብለዋል፡፡
ይህም ስራ ፈጣሪነትን ለማጎልበት እና ዘላቂ ልማትን ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ነው። ከአይኤፍሲ(IFC) ጋር በመተባበር ባንኩ የደረሰበት የትብብር ሰምምነት ለደንበኞች የወደፊት የኢኮኖሚ መሠረት እንደሚጥል አስታውቀዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) የአፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኢትዮጲስ ተፈራ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ አነስተኛና መካከለኛ ቢዝነሶች ለማደግ አስተማማኝ የፋይናንስ ተደራሽነት ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

አይኤፍሲ ከዳሸን ባንክ ጋር የፈጠረው አጋርነት ይህንን እንደሚያሳካ ጠቁመው የአይኤፍሲ(IFC) ከዳሸን ባንክ ጋር ያለው የረጅም ጊዜ አጋርነት በኢትዮጵያ ለግል ዘርፍ እድገት፣ ለስራ ፈጠራ እና ለኢትዮጵያ ልማት የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አይኤፍሲ(IFC) በ2025 የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ በቴሌኮም፣ በአግሪቢዝነስ እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 605 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ያደረገ ሲሆን፣ ከአይኤፍሲ 2030 ስትራቴጂ ጋር በተጣጣመ መልኩ ቁልፍ የትኩረት ዘርፎች በሆኑት አግሪ ቢዝነስ፣ መሠረተ ልማት (ታዳሽ ኢነርጂ፣ ቴሌኮም እና ሎጂስቲክስ)፣ የማኑፋክቸሪንግ (ፋርማሲዩቲካል እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን የሚደግፉ ዘርፎች) እና የቤት ግንባታዎችን ያካትታል።
ዳሸን ባንክ ከዚህ ቀደም የዓለም ባንክ አካል ከሆነው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) በኢትዮጵያ ለሚገኙ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት የፋይናንስ አገልግሎት የመስጠት አቅሙን ይበልጥ ለማሳደግና የፋይናንስ ተደራሽነትን በተሻለ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችለውን የአጋርነት ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡@SECO


