የኢትዮጵያ መንግሥት የ2018 የመጀመሪያ መንፈቅ የሀገር ውስጥ ብድር ወለድ ክፍያ 126.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ወለዱ በስድስት ወራት ለዕዳ ከተመደበው በጀት 64.6% ድርሻ አለው። ከ2017 ተመሣሣይ ወቅት ሲነጻጸር ከ250 በመቶ በላይ ጨምሯል። ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለሀገር ውስጥ ወለድ መንግሥት 36 ቢሊዮን ብር ከፍሎ ነበር።
ያለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት የዕዳ ክፍያ ግዴታ ከ2017 ተመሣሣይ ወቅት አኳያ ሲነጻጸር በሀገር ውስጥ ወለድ እና ፍሬ ብድር ክፍያ ምክንያት እንደጨመረ የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ሪፖርት አሳይቷል።
በሪፖርቱ መሠረት የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት የ2018 የመጀመሪያ መንፈቅ የሀገር ውስጥ ዕዳ ወለዱ 126.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ወለድ ለስድስት ወራት ለዕዳ ክፍያ ከተመደበው 64.6 በመቶ ድርሻ አለው።
መንግሥት ለሀገር ውስጥ ዕዳ የከፈለው ወለድ ከ2017 ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን ከ250 በመቶ በላይ ጨምሯል። በሪፖርቱ መሠረት በ2017 የመጀመሪያ ስድስት ወራት መንግሥት 36 ቢሊዮን ብር ለሀገር ውስጥ ወለድ ከፍሎ ነበር።
የውጭ ዕዳ ወለድ በአንጻሩ በ2018 የመጀመሪያ መንፈቅ ባለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ከነበረበት 11.7 ቢሊዮን ብር መለስተኛ ጭማሪ አሳይቶ 16.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
የሀገር ውስጥ ወለድ ለምን አሻቀበ?
ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የመንግሥት ወጪ እየሰፋ ሲሔድ “ገንዘብ ማተም ተለምዷል” ሲሉ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይናገራሉ። መንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ሲሸጥ የሚከፍለው ወለድ እስከ 2 በመቶ ብቻ ነበር።

በዋንኛነት “የጡረታ ገንዘብን እና የልማት ባንክ ከፍተኛ ገንዘብን” ይጠቀም የነበረ ሲሆን የሚከፈለው ወለድ ዝቅተኛ ነበር። በዚህም ምክንያት ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት “የግል ባንኮች መሳተፍም ትተው ነበር።” ከአምስት ዓመታት ገደማ በፊት ለግምጃ ቤት ሰነድ የሚከፈለው ወለድ “ገበያውን የሚያንጸባርቅ” ሆኖ ከ16 እስከ 18 በመቶ ደርሷል።
እንደ ጀርመን ድምጽ ዘገባ መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለመሙላት ከብሔራዊ ባንክ መበደር ማቆሙ በእርግጥም ለማክሮ ኤኮኖሚ መረጋጋት አዎንታዊ እንደሆነ በገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው ሪፖርት ያደንቃል። ይሁንና የዕዳ ክፍያ ወጪ እንዲጨምር ማድረጉን እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት ማስከተሉን አትቷል።
በሪፖርቱ መሠረት ከ2017 በጀት ዓመት የዕዳ ክፍያ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የወለድ ክፍያ ነው። በዓመቱ መንግሥት 100.6 ቢሊዮን ብር ዕዳ የከፈለ ቢሆንም አብዛኛው ለሀገር ውስጥ ወለድ የዋለ ነው። በዓመቱ 97.53 ቢሊዮን ብር ለሀገር ውስጥ ወለድ ሲከፈል 3.09 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ ውሏል።
መንግሥት የበጀት ጉድለት ባጋጠመው ቁጥር ለመሸፈን ተጨማሪ ለመበደር እንደሚገደድ የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን በዚህም የወለዱ መጠን “በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ” እንደሚሔድ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ብድር ስንት ነው?
የገንዘብ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሠረት እስከ መጋቢት 22 ቀን 2018 ድረስ ያለው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ብድር 51.8 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። የውጭ ብድር 33.5 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ ሲይዝ የቀረው 18.3 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ የሀገር ውስጥ ብድር ነው።
ከሀገር ውስጥ ብድር ከፍተኛውን ድርሻ ማለትም 17.5 ቢሊዮን ዶላር የፌድራል መንግሥት ነው። በገንዘብ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሠረት የተቀረው 800 ሚሊዮን ዶላር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከብሔራዊ ባንክ የተበደሩት ነው።
የመንግሥት የሀገር ውስጥ ብድር እንዲጨምሩ ካደረጉ እርምጃዎች አንዱ የገንዘብ ሚኒስቴር የ10 ዓመት ቦንድ በማውጣት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ የተረከበበት ነው።
የሀገር ውስጥ ብድር እንዲጨምሩ ካደረጉ እርምጃዎች አንዱ የገንዘብ ሚኒስቴር የ10 ዓመት ቦንድ በማውጣት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ መረከቡ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከንግድ ባንክ የተበደረውን 263.3 ቢሊዮን ብር ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 845.3 ቢሊዮን ብር ዕዳ ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ የተቀየረው በጥቅምት 2017 ነበር።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀ አዋጅ የሚወጡት የዕዳ ሰነዶች ከሦስት ዓመታት የችሮታ ጊዜ በኋላ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍለው የሚጠናቀቁ ሲሆን በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በንግድ ባንክ ሥምምነት የሚወሰን ወለድ ይከፈልባቸዋል።
እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 መንግሥት በግምጃ ቤት ቢል 492.3 ቢሊዮን ብር፣ በረዥም ጊዜ ቦንድ እና በግምጃ ቤት ቦንድ 2.2 ትሪሊዮን ብር እንደተበደረ ገንዘብ ሚኒስቴር ለሕግ አውጪው ምክር ቤት ባቀረበው ማብራሪያ አሳይቷል። በአጠቃላይ የመንግሥት የሀገር ውስጥ ብድር 2.7 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 125.8 ቢሊዮን ብር ብድር ሲታከልበት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዕዳ ብር 2.8 ትሪሊዮን ብር ደርሷል።

ለመንግሥት የሚያበድረው ማን ነው?
የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ በሚያደርገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግል ባለወረቶች የመንግሥት የዕዳ ሰነዶችን እንዲገዙ አመቻችቷል። ዋንኛዎቹ ገዥዎች ግን የንግድ ባንኮች ናቸው። የ28፣ የ91 እና የ184 ቀናት የግምጃ ቤት ሰነዶችን እየገዙ የሚያበድሩት ባንኮች “በጣም ከፍተኛ የሆነ ወለድ ከመንግሥት ስለሚያገኙ ለእነሱም ተመችቷቸዋል” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን ያስረዳሉ። “የውጭ ብድር ብዙ ድርድር አለው” የሚሉት የገንዘብ ባለሙያው የሀገር ውስጥ ብድር ለመንግሥትም እንደቀለለው ያምናሉ።
ለ2018 የጸደቀው 1.9 ትሪሊዮን ብር የፌድራል መንግሥት በጀት 277.5 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንደሚገጥመው ይጠበቃል። በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ የበጀት ጉድለቱ 93.6 ቢሊዮን ብር እንደነበር የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ይጠቁማል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት መንግሥት ከታክስ 710 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑት ካፒታል ገቢን ጨምሮ 55.4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከብድር እና እርዳታ በበጀት ድጋፍ መልክ 171 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ሚያዚያ 26 ቀን 2018 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አድርገዋል። በዘጠኝ ወራት የመንግሥት አጠቃላይ ገቢ 1.137 ትሪሊዮን ብር ነው።
በተመሣሣይ ጊዜ ውስጥ መንግሥታቸው የገጠመውን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን 208 ቢሊዮን ብር ከሀገር ውስጥ የመበደር ዕቅድ ነበረው። ይሁንና የተበደረው ከዕቅዱ በላይ 232.4 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ 12.4 ቢሊዮን ብር በግምጃ ቤት ቦንድ የተበደረው ሲሆን ቀሪው 220 ቢሊዮን ብር በግምጃ ቤት ቢል የተወሰደ እንደሆነ የአቶ አሕመድ ሽዴ ሪፖርት ይጠቁማል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ“የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የዋጋ ግሽበትን ከማያባብሱ ምንጮች ወይም ከግምጃ ቤት ሰነድ እና ቦንድ ሽያጭ ከሀገር ውስጥ ብድር በመውሰድ መሸፈን ተችሏል” ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል።
አቶ አሕመድ “የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የዋጋ ግሽበትን ከማያባብሱ ምንጮች ወይም ከግምጃ ቤት ሰነድ እና ቦንድ ሽያጭ ከሀገር ውስጥ ብድር በመውሰድ መሸፈን ተችሏል” ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል። መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲገጥመው ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው የቀጥታ ብድር እንዲቆም ያደረገው ማሻሻያ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴን ጨምሮ በሀገሪቱ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንደ ትልቅ ስኬት የሚያቀርቡት ጉዳይ ነው።@SECO


