በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ መደናገርን ሊፈጥር ስለሚችል ይፋዊው ሰነድ እስኪወጣ ድረስ በአዋጅ ቁጥር 1410/2018 አተገባበር ዙርያ ትግስት እንዲኖር ተጠየቀ፡፡
በኢቢቪ ዘጋቢ
የፍትህ ሚኒስቴር አዲሱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እስኪወጣ ታግሳችሁ ጠብቁ ተብላችኋል፡፡
አዲሱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እስኪወጣ ድረስ ሕዝቡ እና ባለድርሻ አካላት በትዕግስት እንዲጠባበቁ የፍትህ ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓም ለ 64 ዓመታት አገልግሎት ላይ ውሎ የቆየውን የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ የሚተካውን የወንጀል ሥነ- ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1410/2018 ማጽደቁ ይታወሳል።
በዚሁ መሰረት አለ የፍትህ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የፀደቀው ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እና ወጥቶ ሙሉ በሙሉ ወደ ተፈጻሚነት እንዲገባ ለማስቻል የመጨረሻው የቃላት ማስተካከያ እና ሌሎች የሕግ አርትኦት ሥራዎች (Editorial Works) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፍትህ ሚኒስቴር በኩል በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።
ሆኖም በተለያዩ መንገዶች መታዘብ እንደቻልነው ሲል አከለ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ሕጉ ለሕዝብ በይፋ ባልተሰራጨበት ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያት ሲዘጋጁ የነበሩ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ ረቂቅ ሰነዶችን ለተለያዩ ሙያዊና ተቋማዊ አገልግሎቶች እና ስልጠናዎች በተለያዩ አካላት ዘንድ ጥቅም ላይ የማዋል ዝንባሌዎች መኖራቸው ተስተውሏል።
የመጨረሻው የአርትኦት ሥራ ሳይጠናቀቅ ማንኛውንም ይፋዊ ያልሆነ ሰነድ ለሥራ ማስፈጸሚያነትም ሆነ ለሌሎች ተዛማጅ ተግባራት ማዋል በአፈጻጸም ላይ የቃላትና የአንቀጾች አለመጣጣምን እንዲሁም ሌሎች በርካታ ችግሮችን በማስከተል በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ መደናገርን ሊፈጥር ስለሚችል ይፋዊው ሰነድ እስኪወጣ ድረስ ከእንዲህ መሰል አጠቃቀሞች ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የፍትሕ ሚኒስቴር በጥብቅ አሳስቧል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጨረሻው የአርትኦት ሥራ ሲጠናቀቅ ሕጉ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆን ከመሆኑ በተጨማሪ በሚኒስቴሩ ድረ-ገጽና የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ላይ ወዲያውኑ በሶፍት ኮፒ በይፋ የሚጋራ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም ለፍትሕ ሥርዓቱ ወጥነት ሲባል ሕጉ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እስኪወጣ ድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና የሕግ ባለሙያዎች በትዕግሥት እንዲጠባበቁና ሲል ነው መግለጫውን የቋጨው፡፡SECO


