በቅርቡ ከፍተኛ የአመራርና የመልካም አስተዳደር ውዝግብ ውስጥ የገባው ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ፤ አንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮን ከሌላ የፋይናንስ ተቋም በወሰዱት ብድር ወደ 18 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የአክሲዮን ክፍያ ፈፅመዋል የሚል ጥቆማ መውጣቱን ተከተሎ አዳዲስ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛል።
ተቋሙ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ቁጥጥር ስር በወደቀበት፣ የባንኩ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር) ከኃላፊነታቸው በተነሱበት እና 18 የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች በዕገዳ ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት፣ ይህ ይፋ የሆነው መረጃ የባንኩን ውዝግብ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
ኢት-ቢዝነስ ቪው ባገኘው የውስጥ መረጃ መሠረት፤ በባንኩ የቀድሞ አመራሮችና በተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች መካከል የነበረው አለመግባባት መንስኤ የብድር አሰጣጥ፣ የእፎይታ ጊዜ ጥያቄዎችና የብድር አከፋፈል ውሎች ነበሩ። ሆኖም እነዚህ የቀረቡት ክሶች በይፋ ያልተረጋገጡ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው የቁጥጥር እርምጃ በቀጥታ ከዚህ አክሲዮን ግዢ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ያረጋገጠው ነገር የለም።

በቀረበው የግምገማ ሰነድ መሠረት፣ ቢያንስ አንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮን ወደ 18 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የባንኩን አክሲዮን ለመግዛት ያዋሉት ገንዘብ ከሌላ የፋይናንስ ተቋም በብድር የተገኘ ነው። ገንዘቡ ቀጥታ ወደ ግሎባል ባንክ በመዛወር የአክሲዮን ግዢው መፈፀሙን ምንጮች ጠቁመዋል።
ይህ አሰራር በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ የባለቤትነት ድርሻ ለመያዝ የሚደረጉ የገንዘብ ምንጮችን ግልጽነት እና ባለአክሲዮኖች በቦርድ ውሳኔዎች፣ በመልካም አስተዳደርና በብድር ፖሊሲዎች ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ አሳሳቢ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

ከአክሲዮን ግዢው ባሻገር፣ አንዳንዶች ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች በራሳቸው ወይም ከእነሱ ጋር ቁርኝት ባላቸው ድርጅቶች ስም ያልተከፈሉ ከፍተኛ ብድሮች እያሉባቸው ተጨማሪ የብድር አቅርቦትና የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ እንዲደረግላቸው ጫና አድርገዋል የሚሉ ጥቆማዎች ወጥተዋል።
የባንኩ የቀድሞ አመራሮች እነዚህን ጥያቄዎች በመቃወማቸው ምክንያት በአመራሩና በባለአክሲዮኖቹ መካከል ከፍተኛ አለመግባባት መፈጠሩ ተገልጿል።
የቀረቡት ክሶች እውነትነት ካላቸው፣ በተዛማጅ ወገኖች ብድር እና በጥቅም ግጭት ላይ ትልቅ ስጋት የሚፈጥሩ ናቸው።
ይህ ውዝግብ የተከሰተው ብሔራዊ ባንክ በግሎባል ባንክ ላይ ባካሄደው ልዩ ኢንስፔክሽን መሠረት በኮርፖሬት አስተዳደር፣ በብድር፣ በሰው ሀብት፣ በውጭ ምንዛሪና በፋይናንስ አስተዳደር ላይ ክፍተቶች ማግኘቱን ተከተሎ ባስተላለፈው ውሳኔ ነው።
ተቆጣጣሪ አካሉ 18 ከፍተኛ አመራሮችን ከሥራ ያገደ ሲሆን፣ የቀድሞውን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተስፋዬ ቦሩን ከኃላፊነታቸው አንስቷል። በተጨማሪም ተስፋዬ በሚመጣው አምስት ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ በሚገኝ ማንኛውም የፋይናንስ ተቋም ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት እንዳያገለግሉ እገዳ እንደተጣለባቸው ይታወሳል::SECO


