የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው 7ኛው አገራዊ ምርጫ ለውድድር የሚቀርቡ ዕጩዎች እና መራጮች በዲጂታል አማራጭ መመዝገብ የሚችሉበትን የድረ-ገጽ እና የ”ምርጫዬ” መተግበሪያ ይፋ አደረገ።
ቦርዱ የዲጂታል አማራጮቹ በስድስት አገር በቀል ቋንቋዎች እንዲያገለግሉ ተደርገው መዘጋጀታቸውን አስታውቋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ይህ የዲጂታል ሥርዓት የሚያገለግለው ለምዝገባ ሂደት ብቻ ነው። ማንኛውም መራጭ በዲጂታል አማራጭ ቢመዘገብም፣ ድምፅ ለመስጠት ግን እንደወትሮው ሁሉ በተመዘገበበት የምርጫ ጣቢያ በአካል መገኘት እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።
በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የዕጩዎች ምዝገባ ከፊታችን አርብ ጥር 1 ቀን እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን፣ የመራጮች የቴክኖሎጂ ምዝገባ ደግሞ ከጥር አጋማሽ እስከ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። መራጮች “ምርጫዬ” የተሰኘውን መተግበሪያ በሞባይል ስልካቸው በመጫን ወይም ቦርዱ ባዘጋጀው ድረ-ገጽ በመጠቀም ምዝገባ ማከናወን ይችላሉ።
የዘንድሮው አገራዊ ምርጫ የድምፅ መስጫ ዕለት ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።@SECO


