በዓለምሰገድ እስጢፋኖስ
ኢትዮ ቴሌኮም ዘመነኛ የዲጂታል ማሰራጫ አስተዋውቋል።
‘ቴሌ ስትሪም’ የሚሰኘውና በርካታ የቴሌቪዥን ቻነሎችንና ዲጂታል ይዘቶችን ያቀፈው ዲኮደር መሰል አገልግሎትን ነው።
ከቴሌቪዥን ጋር ተያይዞ የሚሰራው ቴሌስትሪም የጣራ ላይ ሳህን የማይፈልግ፣ በሲም ካርድ፣ ዋይፋይ፣ ወይም ብሮድባንድ የሚሰራ ነው።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዳስታወቁት ኩባንያው በዛሬው ዕለት የሚዲያ ስነ-ምህዳር የሚቀይር የ”ቴሌስትሪም የተሰኘ በኢንተርኔት የሚሰራ የይዘት ስትሪሚንግ አገልግሎት እንዲሁም የመደበኛ ብሮድባንድ አገልግሎት አሰጣጥን ሙሉ በሙሉ የሚያዘምን የፊክስድ ብሮድባንድ (ዋይ ፋይ) አገልግሎት ንክኪ አልባ ዲጂታል አሰራር ይፋ አድርጓል።

የ“ቴሌስትሪም” አገልግሎት፤ የዜጎችን የዲጂታል አኗኗር ዘይቤ ከማዘመን ባለፈ ለተጠቃሚዎች የላቀ የቴክኖሎጂ ተሞክሮን የሚያበረክትና የሀገሪቷን የሚዲያና መዝናኛ ስነ-ምህዳር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሆነ ተናግረዋል።
የቴሌስትሪም አገልግሎት፤ በኩባንያችን የፋይበር እና የቴሌ ክላውድ መሰረተ ልማት የሚቀርብ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ዝቅተኛ መዘግየት እና እጅግ የላቀ የስርጭት ጥራት ያለው እንደሆነና ተጠቃሚዎች ያለ ሳተላይት ዲሽ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ይዘቶችን በቤታቸው ባለው የብሮድባንድ ኢንተርኔት ዋይ ፋይ በቀላሉ እንዲመለከቱ ያስችላል ብለዋል።
ከ60 በላይ የቀጥታ ስርጭት ቻናሎችን እና ከ350 በላይ በፍላጎት የሚታዩ ቪዲዮዎችን የያዘው የቴሌስትሪም አገልግሎት፤ በመደበኛ ብሮድባንድ፣ በሲም ካርድ እንዲሁም የ‘Set Top Box’ (STB) መሣሪያን በመጠቀም የስትሪሚንግ አገልግሎት ከማቅረብ በተጨማሪ ስማርት ያልሆኑ ቴሌቪዥኖችን ወደ ስማርትነት በመቀየር ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ቴሌስትሪም ለሀገሪቱ የሚዲያና የመዝናኛ ስነ-ምህዳር ተዋንያን አዲስ የዕድገት አድማስ የከፈተ ነው ሲሉ የተናገሩት ፍሬህይወት ታምሩ በዚህም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ የፕሮዳክሽን ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የፊልም አዘጋጆችና ተዋንያን እንዲሁም በትምህርት፣ በጤና እና በማህበረሰብ እሴት ግንባታ ላይ የሚሰሩ አካላት የሀገሪቱን ብሄራዊ እሴት የጠበቁ ይዘቶቻቸውን በስፋት ተደራሽ የሚያደርጉበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሰፊ ስትራቴጂያዊ ዕድል እንደተፈጠረ አስታውቀዋል።
አገልግሎቱ በኢትዮጵያ እስካሁን የነበረውን የሳተላይት ዲሽ ጥገኝነት የሚቀይርና እጅግ የላቀ አማራጭ ይዞ የመጣ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን ስርጭቶችን በአገር ውስጥ በሚገኘው የኩባንያው ቴሌ ክላውድ በማስተናገድ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ዜናዎችን፣ የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራሞችን፣ ትምህርታዊ ይዘቶችን፣ ፖድካስቶችን እና ፊልሞችን ያለ ምስል መቆራረጥ ለማስተላለፍ ያስችላል ተብሏል።@SECO


