የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ80 ዓመታት ጉዞ ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር አህጉራዊ ምልክትነቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በማስመልከት በተዘጋጀ መድረክ ላይ እንደተገለጸው ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ተጀምሯል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንዳስታወቁት የግንባታ ሂደቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ በ 760 ሚሊየን ዶላር ወጪ ወደ ስራ ተገብቷል።
በፕሮጀክቱ ግንባታ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ አርሶ አደሮች ዘላቂነት እንዲቋቋሙ በማድረግ፣ ዘመናዊ ቪላ፣የማህበራዊ አገልግሎት፣የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎችም መሰረታዊ ግብአት ተሟልቶላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ80 ዓመታት ጉዞ ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር አህጉራዊ ምልክትነቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ ደግሞ የተናገሩት የአየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ናቸው።
አየር መንገዱ ባለፉት ስምንት አስርት ዓመታት የዕድገትና ስኬት ጉዞዎችን በማድረግ ዛሬ ያለበት ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካይሮ አንድ ብሎ በረራ የጀመረውን የዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት አሁን ላይ መዳረሻውን ወደ 145 ማስፋቱን አስታውቀዋል።
በዚህም 147 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት በመሆን በዓመት ከ20 ሚሊየን በላይ መንገደኞች ማስተናገድ የሚያስችል አቅም መገንባቱን ገልጸዋል::@SECO


