በኢቢቪ ዘጋቢ
የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በሰባተኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ላይ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምልከታ፣ በቀጣይ የምርጫውን ተዓማኒነትና ቅልጥፍና ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዱ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ አሳስቧል።
በዛሬው ዕለት በተሰጠዉ እና ቅዳሜ ገበያ በተከታተለችዉ በዚህ መግለጫ ላይ በቀድሞ የኬንያዉ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያት የሚመራዉ ታዛቢ ቡድኑ በአንድ ምርጫ ጣቢያ እስከ 1,500 መራጮችን ለማስተናገድ የተቀመጠው ገደብ እጅግ ከፍተኛ መሆኑንና ይህም የሥራ ጫናን በትክክል ለመቆጣጠር ፈታኝ እንደነበር ጠቁሟል።
የታዛቢ ቡድኑ መሪ በሰጡት ማብራሪያም የሥራ ጫናን በአግባቡ ለመምራትና የሂደቱን ቅልጥፍና ለማረጋገጥ በአንድ ጣቢያ የሚመደቡ መራጮች ቁጥር በድጋሚ ሊፈተሽና ደረጃውን የጠበቀ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፣ በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1,500 መራጮች መመደባቸው ያለጥርጥር እጅግ ከፍተኛ ቁጥር መሆኑንና ይህንን የአሠራር ሂደት ማሻሻል የምርጫውን ጥራት ይበልጥ እንደሚያሳድገው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም የድምፅ መስጫ ምስጢራዊነትን እና የመራጮችን ምቹ እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማረጋገጥ የድምፅ መስጫ ሳጥኖች እና የገበታዎች አቀማመጥ ወጥ የሆነ ቅርፅ ሊኖራቸው እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን፣ ሴቶች በህዝብ ቁጥር ሰፊውን ድርሻ ቢይዙም በመራጮች ምዝገባ ወቅት የነበራቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ይህንን ክፍተት ለመሙላት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።
አሁሩ ኬንያታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ሂደት በገለልተኝነትና በባለሙያነት ለመምራት ያሳየውን ቁርጠኝነት ያደነቁ ቢሆንም፣ ሂደቱን ይበልጥ አካታች ለማድረግ በእነዚህ መዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።@seco


