የዓለማችን ዋነኛው የዲጂታል ገንዘብ ቢትኮይን፣ በ2026 ዓ.ም እያሳየ ካለው የዋጋ መዋዠቅ አንጻር፣ የወደፊት ጉዞው እንደ ወርቅ ሁሉ “ድል እና ፈተና” የተሞላበት ሊሆን እንደሚችል የገበያ ተንታኞች እየገለጹ ነው። ቢትኮይን ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ከ50 በመቶ በላይ ዋጋ ማጣቱ ለባለሀብቶች ስጋት ቢፈጥርም፣ የኤክስቼንጅ ትሬድ ፈንድ (ETF) እንቅስቃሴዎች በቢትኮይን ላይ አዲስ ተስፋን እየፈጠሩ ይገኛል።
የብሉምበርግ ኢንተለጀንስ የኢቲኤፍ (ETF) ተንታኝ ኤሪክ ባልቹናስ እንደገለጹት፣ የቢትኮይን ኢቲኤፍ ባለሀብቶች የወርቅ ኢቲኤፍ የ22 ዓመታት ታሪክን እንደ ማጣቀሻ ሊወስዱት ይገባል። በ2004 ዓ.ም የወርቅ ኢቲኤፍ ሲጀመር የወርቅ የገበያ ዋጋ ወደ 28 ትሪሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ያስታወሱት ተንታኙ፣ ቢትኮይን እና ወርቅ በገበያ ላይ ያላቸው መስተጋብር ተመሳሳይነት እንዳለው ተናግረዋል። ሁለቱም ንብረቶች ምንም ዓይነት የወለድ ገቢ የማይሰጡ፣ ነገር ግን የባለሀብቶችን ስሜት መሠረት በማድረግ ዋጋቸው የሚወሰን መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለሙያው አክለውም፣ ቢትኮይን ኢቲኤፎች ልክ እንደ ወርቅ “አስደናቂ የዋጋ ጭማሪ፣ አሳማሚ የወጋ መቀነስ እና የባለሀብቶችን ትዕግስት የሚፈታተኑ የማገገሚያ ዑደቶች” ሊያሳልፉ እንደሚችሉ ተንብየዋል። በተለይም የዓለማችን ትልቁ የሀብት አስተዳዳሪ ድርጅት “ብላክ ሮክ” በቢትኮይን ገበያ ላይ ያለው የበላይነት፣ ዋጋው በድንገት ወደ ላይ እንዲያሻቅብ ወይም እንዲያሽቆለቁል የማድረግ አቅም እንዳለው ተጠቁሟል።
ይሁን እንጂ የቢትኮይን እና የክሪፕቶ ገበያ ተሳታፊዎች በኢቲኤፎች ላይ ያለው ፍላጎት አሁንም ጠንካራ እንደሆነ ይናገራሉ። የ ኤክስ ኤስ ኮም የንግድ ልማት ኃላፊ ሳይመን-ፒተር ማሳብኒ እንደገለጹት፣ “የተቋማት ፍላጎት የቢትኮይን አንዱ ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ ቀጥሏል።” አያይዘውም፣ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ኩባንያዎች ዲጂታል ንብረቶችን በፖርትፎሊዮዎቻቸው ውስጥ እያካተቱ መሆኑ፣ በገበያው ላይ የሚታየውን የሽያጭ ግፊት ለመቀነስ እንደረዳ ገልጸዋል።SECO


