በመካከለኛው ምስራቅ በኢራን እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለው ወታደራዊ ፍጥጫ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ንግድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳረፉን ቀጥሏል።
በተለይም በሆርሙዝ የባሕር ስርጥ አካባቢ የኢራን የጦር ጀልባዎች በአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ በሚጓዙ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ትንኮሳ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ የደህንነት ስጋቱ በነዳጅ ማጓጓዣ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አስከትሏል።
የባልቲክ ኤክስቼንጅ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ ቻይና የሚደረግ የነዳጅ ጭነት የየቀን ኪራይ በ5.1 በመቶ በማደግ 129,000 ዶላር ደርሷል፤ ይህም ካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ህዳር ወር ወዲህ የታየ ከፍተኛው የዋጋ መጠን ነው።
ለዚህ የዋጋ መናር ዋነኛው ምክንያት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ “ግዙፍ የባሕር ኃይል ጦር” እንደሚላክ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ሲሆን፣ ይህም የብሬንት የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ሳምንት 70 ዶላር እንዲነካ አድርጎታል።
ምንም እንኳን በሳምንቱ መጨረሻ ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር የንግግር ተስፋ መኖሩን በመግለጽ ውጥረቱ ጋብ ያለ ቢመስልም፣ በዘርፉ ያለው የመርከቦች እጥረት ግን ዋጋው እንዳይቀንስ አድርጎታል። በአሁኑ ወቅት በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ነጻ መርከቦች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ፣ የመርከብ ባለቤቶች በዋጋ የመደራደር አቅማቸው እጅግ ከፍተኛ ሆኗል።
በሌላ በኩል፣ የትራምፕ አስተዳደር ከኢራን የሚመነጨውን የነዳጅ ፍላጎት በቬንዙዌላ ምርት ለመተካት ቢሞክርም፣ የቬንዙዌላ የነዳጅ ምርትን የማሳደግ ሂደት ከታሰበው በላይ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኝቷል።
እንደ ፎርቴክሳ ያሉ የንግድ ተንታኞች እንደሚጠቁሙት፣ የጦርነት ስጋቱ “ፕሪሚየም” ክፍያ ለጊዜው ሊቀንስ ቢችልም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የመርከቦች አቅርቦት ጥረት እና የንግድ መስመሮች መርዘም የጭነት ዋጋው በዚህ ዓመት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀጥል ሊያደርገው ይችላል።@SECO


