አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችና አርሶ አደሮች እንደ ከብት ያሉ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በመያዣነት በመጠቀም የባንክ ብድር እንዲያገኙ ለማስቻል የተጀመረው መርሃ-ግብር፣ በመሠረተ ልማት እና በዕውቀት ክፍተት ምክንያት በሙከራ ደረጃ መጓተቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
የባንኩ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ ባንኮች እንደ መያዣ የተረከቧቸውን ከብቶች የሚንከባከቡበት ቦታና በቀጥታ የሚሸጡበት የመስመር ላይ ገበያ አለመኖር ለሂደቱ መቆም ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ እስካሁን ከ285,000 በላይ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በባንኩ የመረጃ ቋት መመዝገባቸውንና ባንኮችም ከዘንድሮ ጀምሮ መርሃ-ግብሩን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መታዘዛቸው ተመልክቷል።
በተያያዘም የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያው በባንኮች ላይ ጉዳት እንዳላደረሰ የጠቀሱት ምክትል ገዥው፣ የባንኮች አጠቃላይ ትርፍ ስድስት እጥፍ አድጎ 91 ቢሊዮን ብር መድረሱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።@SECO


