የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በአለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ላይ ሊተገብር ባሰበው አዲስ መመሪያ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የሁለት እና የሦስት ዓመታት የሽግግር ጊዜ ሊሰጥ እንደሚችል ፍንጭ መስጠቱ ተዘግቧል።
ሚኒስቴሩ በቅርቡ ባወጣው መመሪያ መሠረት፣ ማንኛውም በአገሪቱ የሚንቀሳቀስ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ካሪኩለም ማለትም የታሪክ፣ የቋንቋ እና የዜግነት ትምህርቶችን በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ እንዲያካትት ያስገድዳል።
በተጨማሪም የተማሪዎች ስብጥር ቢያንስ 30 በመቶ የውጭ ዜጎች እንዲሆኑ የሚደነግግ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።
ይህ መመሪያ ይፋ መደረጉን ተከትሎ እንደ ዋን ፕላኔት፣ ብሪቲሽ እና ካናዲያን እና ፍሊፐር ኢንተርናሽናል ያሉ ታዋቂ ትምህርት ቤቶች ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ትምህርት ቤቶቹ መመሪያው በአንድ ጊዜ ተግባራዊ መደረጉ በተማሪዎች፣ በወላጆች እና በትምህርት ቤቶቹ የዝግጅት ሂደት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ይፈጥራል የሚል ስጋት አቅርበዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባለፈው ሳምንት ከባለድርሻ አካላት ጋር አድርጓል በተባለዉ ውይይት፣ መመሪያው የአገሪቱን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የወጣ በመሆኑ የማይቀየር መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሆኖም ትምህርት ቤቶቹ ራሳቸውን ከአዲሱ አሰራር ጋር እንዲያስማሙ የሁለት እና የሦስት ዓመታት የሽግግር ጊዜ ሊፈቀድላቸው እንደሚችል ካፒታል መንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የማስተማሪያ ቋንቋ እና የይዘት ማቀናጀት
ሚኒስቴሩ አክሎ እንደገለጸው፣ ትምህርት ቤቶቹ ይዘታቸውን ከሀገሪቱ ካሪኩለም ጋር ቢያቀናጁም፣ የማስተማሪያ ቋንቋቸው ግን እንደቀድሞው በእንግሊዝኛ እንዲቀጥል ይፈቀድላቸዋል ነዉ ተባለው።@SECO


