አምባሳደር ቆንጂት ስነ ጊዮርጊስ – የዲፕሎማሲ እናት (ከ1932 እስከ 2018)

 
በአለምሰገድ እስጢፋኖስ

የሙያ አጋሮቻቸው ሁሉ ‹‹ተንቀሳቃሿ የአፍሪካ ጉዳዮች ኢንሳይክሎፒዲያ ብለው ይጠሯቸዋል። ለ52 ዓመታት ያህል የኖሩበት የዲፕሎማሲው ዓለም ባለረጅም ዘመን አገልግሎታቸው አፍሪካዊት ዲፕሎማት አሰኝቷቸዋል … አምባሳር ቆንጂት ስነ ጊዮርጊስን!

እርሳቸው ለዚህ ስኬት የበቁት ግን በቀላሉ አልነበረም። ‹‹ለሴት የሚሆን ሥራ አይደለም›› ከሚለው አስደንጋጭ እሳቤ ጀምሮ ሙሉ የሕይወት ጊዜን ለሙያ (ለሥራ) እስከመሰዋት የደረሱ ፈተናዎችን ተቋቁመው እንጂ።

ቆንጂት በ1932 ዓ.ም ሐረር ውስጥ ተወለዱ። አስተዳደጋቸው በራስ የመተማመንና የነፃነት ስሜት እንዲኖራቸው ዕድል ሰጥቷቸዋል። ለዚህም የእናታቸው የታላቅ ወንድሟ ድርሻ የጎላ ነበር። በተለይ ታላቅ ወንድማቸው እንደታላቅነቱ በቆንጂት እንቅስቃሴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ይልቅ ነፃነትን ከኃላፊነት ጋር ይሰጣቸው ስለነበር ወንድማቸው የጣለባቸውን እምነት እንዲያከብሩ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እንዲያስቡ፣ ውሳኔአቸውን ራሳቸው  እንዲወስኑ፣ በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑ በኃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል።

ቆንጂት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ  በኋላ ከእህታቸው ጋር ወደ ለንደን፣ እንግሊዝ በማቅናት ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ የህይወተወ ታሪካቸው ያሳያል፡፡

በለንደን ቆይታቸውም  የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ለማጥናት ለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪአቸውን ማግኘት ችለዋል፡፡

ትምህርታቸውን ከለንደን አጠናቀው ከመጡ በኋላ በወቅቱ የሥራ ምደባ ወደሚካሄድበት ቢሮ በመሄድ የተማሩት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስለሆነ መሥራት የሚፈልጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እንደሆነ ተናገሩ። ማመልከቻቸውን ያቀረቡላቸው የሥራ ኃላፊ ግን ‹‹ … እሱ ለሴት የሚሆን ቦታ አይደለም›› የሚል ምላሽ ሰጧቸው። ቆንጂት በምላሹ ቢደነግጡም የግድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግባት እንዳለባቸው ወሰኑ። ምላሹ እንደተለመደው ቢሆንም ቆንጂት ግን በየቀኑ ወደ ሚኒስቴሩ እየሄዱ ይቀመጡ ነበር። ከዚያም ‹‹ይቺ ልጅ አልለቀቀችንም፤ ደብዳቤ ተጽፎላት ትግባ› ተብሎ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) ከመመሥረቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ1954 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለመቀላቀል ቻሉ፡፡

ቆንጂት የተመደቡት በሚኒስቴሩ የተባበሩት መንግሥታት ክፍል ውስጥ ነበር። ከሦስት ዓመታት በኋላ ዕድገት አግኝተው በሁለተኛ ፀሐፊ ማዕረግ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ጽሕፈት ቤት ውስጥ እንዲሰሩ  ተመደቡ። ቆንጂት መሥራት የሚፈልጉት ዋና የዲፕሎማሲ ሥራ እንጂ በአስተዳደር ሥራዎች ላይ ባለመሆኑ ሕልማቸውን ለማሳካት ጥረታቸውን  ቀጠሉ። በዚህም በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ቡድን ውስጥ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ጉዳዮች ኦፊሰር ሆነው መሥራት ጀመሩ። ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለ10 ዓመታት ያህል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ገለልተኛ አገራት መምሪያ ውስጥ መስራት ችለዋል። በመቀጠልም በ1970ዎቹ ጀኔቫ፣ ስዊዘርላንድ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ምክትል ተወካይ ሆነው ተመደቡ ለአስር ዓመታትም ማገልገል ችለዋል።

ከ28 ዓመታት አጠቃላይ የዲፕሎማሲ አገልግሎት በኋላ እዚያው ጀኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚመልዕክተኛና በኦስትሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እንደተሾሙ አዲስ ዘመን በሰኔ 2012 እትሙ አስነብቧል።

 በመቀጠልም ከመጋቢት 1984 ዓ.ም ጀምሮ በካናዳ፣ በሜክሲኮና በእሥራኤል የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እስከ ነሐሴ 1987 ዓ.ም ድረስ ሠርተዋል። ወዲያውኑ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ ተሹመው ነበር።

ከአንድ ዓመት በኋላ በግብጽ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ተሹመው ከአራት ዓመታት በላይ አገልግለዋል። ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አባባ ተመልሰው ለሁለተኛ ጊዜ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ጄነራል ዳይሬክተር ሆነው እንዲሠሩ ተሹመው ሠርተዋል።

በ1998 ዓ.ም በኦስትሪያ ፌዴራል ሪፐብሊክና በቪየና በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ በድጋሚ ተሾሙ። ከመስከረም ወር 2002 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በክብር በጡረታ እስከተሰናበቱበት ድረስ በአፍሪካ ሕብረት (African Union) እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገራቸውን በትጋት አገልግለዋል።

አምባሳደር ቆንጂት በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በነበሩበት ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጣና አወቃቀሩም የተቋሙን ዓላማዎች በሚያሳካ መልኩ እንዲደራጅ (ወደ ‹‹የአፍሪካ ሕብረት›› እንዲለወጥ) ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም ለአምባሳደር ቆንጂት ደማቅ የስንብትና የምስጋና መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ሽኝት አድርጎላቸዋል፤ አመስግኗቸዋል። በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የነበሩት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በስንብት/ምስጋና መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹ … አምባሳደር ቆንጂት ከአፍሪካ ምርጥ ሴት ልጆች መካከል አንዷ ናቸው። አምባሳደር ቆንጂት አገራቸውንና አህጉራቸውን ከልብ የሚወዱ ዲፕሎማት ናቸው›› በማለት አምባሳደሯ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር የታገሉ አንጋፋ ባለውለታ እንደሆኑ መስክረዋል።   

አምባሳደር ቆንጂት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እንዲሻሻል በተለይም የአፍሪካ አዳራሽ (Africa House) ተብሎ የሚታወቀው የኮሚሽኑ ክፍል አፍሪካዊ ማንነትን የሚንፀባርቅ ሙዚየም እንዲሆን የተጫወቱት ሚና የሚዘነጋ እንዳልሆነ የኮሚሽኑ የቀድሞው ዋና ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔዝ ተናግረዋል።

የቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአሁኑ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ ኣድሓኖም ‹‹ … አምባሳደር ቆንጂት ወደ 53 ዓመታት በተጠጋው አገልግሎታቸው ሕዝብን በማገልገል ስለሚገኝ ክብርና ኩራት አስተምረውናል። በረጅም ዓመታት አገልግሎታቸውና በካበተ ልምድ ባለቤትነታቸው ምክንያት ‹የአፍሪካ ጉዳዮች ኢንሳይክሎፒዲያ (Encyclopedia of African Affairs)› እንላቸዋለን። አፍሪካ በዲፕሎማሲው መስክ ወደፊት እንድትራመድ በትጋት ሲሠሩ የኖሩ ጠንካራና ልዩ ሰው ናቸው …›› በማለት ስለአምባሳደር ቆንጂት አበርክቶ ተናግረዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ለረጅም ዓመታት አገልግሎታቸው ሽልማቶችን አግኝተዋል። ለአብነት ያህል በጥር ወር 2011 ዓ.ም ለረጅም ዘመናት የዲፕሎማሲ አገልግሎታቸው ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የምስጋናና የእውቅና ሰርተፊኬት ተቀብለዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2008 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል።

አንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ  በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 29/2018 ዓ.ምከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።@SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

ኢትዮ ቴሌኮም ሦስት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን ሾመ

አዲስ መዋቅር አስተዋውቋል የኢትዮ ቴሌኮም ሦስት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ...

እስራኤል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አገሯ እንዳይገባ አገደች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አውሮፕላን በበረራ ሰራተኛው ምክንያት ወደ...

የፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌ ‹‹ብዕርና ባሩድ›› መጽሐፍ ገበያ ላይ ዋለ

ፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌ ‹‹ብዕርና ባሩድ›› መጽሐፍ በሀገር ውስጥ፣ በአውሮፓ...

ግብፅ በጅቡቲ በወደብና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያላትን ተሳትፎ ልታፋጥን ነው  

የካይሮ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን እንደማያስደስት ተነግሯል የግብፅ የልዑካን ቡድን በጅቡቲ ዋና...

Popular Categories