ዓለም በኢራን የአሜሪካ እና የእስራኤል ጦርነት ባስከተለው ወጪ ሲናጥ አንዳንድ ኩባንያዎች በምትኩ ከፍተኛ ትርፍ እያስመዘገቡ ነው።
በግጭቱ የተነሳው አለመረጋጋት እና ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን በመዝጋቷ የኑሮ ውድነትን እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ኩባንያዎች ትርፋማ እንደሆኑ የሚወጡ ዘገባዎች እያሳዩ ነው።
የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት ለአውሮፖ ነዳጅና ጋዝ አቅራቦ ኩባንያዎች ሲሳይ ይዞ መጥቷል ሲል ዘገባ ያወጣው ቢቢሲ ነው።
በጦርነቱ እስካሁን ድረስ ትልቁ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ የኢነርጂ ዋጋ መጨመር ነው።
የእንግሊዙ የነዳጅ ድርጅት ቢፒ በዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ትርፍ ከእጥፍ በላይ ወደ 3.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቋል።
በተመሳሳይ ሼል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የትርፍ መጠኑ ወደ 6.92 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።
ሌላኛው ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያ ቶታልኢነርጂስ በነዳጅ እና በኢነርጂ ገበያዎች ላይ በሚታየው ተለዋዋጭነት ምክንያት ትርፉ በ2026 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአንድ ሶስተኛ ከፍ ብሏል፣ ይህም ትርፉ ወደ 5.4 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ነው የገለጸው።
በፋይናንስ ዘርፉ ደግሞ ባንኮች በኢራን ጦርነት ወቅት ትርፋቸው ጨምሯል።
ጄፒ ሞርጋን በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ሪከርድ የሆነ 11.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ ባንኩ በአጠቃላይ በየሩብ ዓመቱ ሁለተኛውን ከፍተኛ ትርፍ ማግኘት እንደቻለ አስታውቋል።
በቀሪዎቹ ስድስት ትላልቅ ባንኮች (ባንክ ኦፍ አሜሪካ፣ ሞርጋን ስታንሊ፣ ሲቲግሩፕ፣ ጎልድማን ሳችስ እና ዌልስ ፋርጎ እንዲሁም ጄፒ ሞርጋንን) ጨምሮ – ትርፉ በሙሉ በዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
በአጠቃላይ፣ ባንኮቹ በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ 47.7 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ እንዳገኙ ሪፖርት አድርገዋል።@seco


