የሶሻል ሚዲያ (ማኅበራዊ ሚዲያ) አጠቃቀም ላይ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች ክልከላ እንዲደረግ በመንግሥት የተሰየመ ልዩ ኮሚሽን ምክረ-ሐሳብ አቀረበ።
የኮሚሽኑ መርማሪ ሊሳ ኤንግሉንድ ክራፍት ከሀገሪቱ የማኅበራዊ ጉዳይና የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ያኮብ ፎርስሜድ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የዕድሜ ገደብ መጣሉ የሚያስገኘው ጥቅም ታዳጊዎች ያለገደብ ከሚያገኙት ነፃ ዕድል ይልቅ በእጅጉ እንደሚበልጥ አስታውቀዋል።
ይህ አዲስ ሕግ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ የዕድሜ ማረጋገጫ የማድረጉን ኃላፊነት የሶሻል ሚዲያ ኩባንያዎቹ ራሳቸው እንዲወጡት ተደርጎ እንደሚቀረጽም ተገልጿል።
ሚኒስትሩ ያኮብ ፎርስሜድ በበኩላቸው፣ “አንድን ሙሉ ትውልድ ስልኮች ላይ ለሚደረግ ማለቂያ የሌለው ‘ስክሮሊንግ’ አሳልፈን እየሰጠን ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። አክለውም ስክሪኖችና ሶሻል ሚዲያ በታዳጊዎች ጤና ላይ እያሳደሩት ያለው ተጽዕኖ የዘመናችን ትልቁ ፈተና መሆኑን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት በስዊድን ሕግ ሕፃናት በ13 ዓመታቸው የወላጅ ፈቃድ አግኝተው የሶሻል ሚዲያ አካውንት መክፈት የሚችሉ ሲሆን፣ አዲሱ ምክረ-ሐሳብ ግን ይህንን አሠራር ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት በሕፃናት ሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ጎረቤት ሀገር ኖርዌይ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች ክልከላ የሚጥል የሕግ ረቂቅ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለፓርላማ እንደምታቀርብ ያስታወቀች ሲሆን፣ አውስትራሊያም በተመሳሳይ ከ16 ዓመት በታች ላሉ ታዳጊዎች የጣለችውን የዓለማችን የመጀመሪያውን የሶሻል ሚዲያ እገዳ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።


