በባንኮች ላይ ተጥሎ የነበረው  የብድር ገደብ ሙሉ በሙሉ ተነሳ

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሰባተኛ ስብሰባው አስመልክተው  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ገደብን (credit cap) ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን በመጠቀም በወለድ ምጣኔ ላይ ተመስርቶ ወደሚሰራ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እስኪሸጋገር ድረስ በጊዜያዊነት ሲጠቀምበት እንደቆየ አስታውሰው በአሁኑ ወቅት የብድር ገደቡ የታቀደለትን ዓላማ ያሳካ በመሆኑ፣ ኮሚቴው ገደቡ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ምክረሃሳብ አቅርቦ ቦርዱ እንዳጸደቀው አስታውቀዋል፡፡

የብድር ገደብ መነሳት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ለውጥ ሳይሆን የወለድ ተመንን መሠረት ያደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ወደ ተሳካ ሽግግር በመድረሱና ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ውጤታማ እየሆኑ በመምጣታቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋሙን ለማስቀጠል በፖሊሲ ማዕቀፉ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን መጠቀሙን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ኮሚቴው የብድር ዕድገት ገደብ መነሳትን ተከትሎ ተመጣጣኝ የሆነ የጥብቅ ፖሊሲ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግ መሆኑን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋሙን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመገንዘቡ ፣ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔን በ1.0 መቶኛ ነጥብ (ከ15 በመቶ ወደ 16 በመቶ) ለማሳደግ እና የ ± 3 የመቶኛ ነጥብ ክልል (band) ሳይለወጥ እንዲቆይ ምክረ ሃሳብ አቅርቦ በቦርዱ መጽደቁን አስረድተዋል።

የብድር ዕድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያካሂደው መደበኛ ግምገማ መሠረት የእያንዳንዱ ባንክ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ ጥመርታ (loan-to-deposit ratio) ላይ በመመርኮዝ የተለየ የመጠባበቂያ ተቀማጭ(targeted reserve requirement) ይተገበራል ብለዋል፡፡

ሌላኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ኮሚሽን ምጣኔ ከ2.5 በመቶ ወደ 1.5 በመቶ (በ1 የመቶኛ ነጥብ) እንዲቀንስ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ለባንኮች እንዲሸጡ የሚጠየቀው 50 በመቶ (FX surrender requirement) ወደ 30 በመቶ ዝቅ ሊል ችሏል፡፡

ኮሚቴው በመስከረም 2019 ዓ.ም. መጨረሻ እንደገና ለመሰብሰብ፣ አስፈላጊ ሁኔታ ከተፈጠረም ከዚያ ቀደም ብሎ ለመሰብሰብ እንደተስማማ  ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡seco

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 220 ቦታዎች የሊዝ ጨረታ አወጣ

​የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በዘጠኝ ክፍለ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

Popular Categories